Parent's Corner
የልጆች አስተዳደግ በውጭው ዓለም*
በላቸው ጨከነ (ዶ/ር)
ልጆች "ብዙ ተባዙ" በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ከእግዚአብሔር የሚገኘ በረከቶች ናቸው። ቅዱስ ዳዊት "ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎችናችው"(መዝ ፻፳፮፥፫) እንዳለ። ቅዱሳን ፣ ጻድቃን፣ ጳጳሳት ፣ ካህናት፣ ነገሥታት እና መሣፍንት የሚገኙት ከዚሁ አምላካዊ በረከት ነው። በአለንበትዘመን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ፣ የኑሮ ጫና እና የዓለም መቀራረብ የልጆችን አስተዳደግ ለሁሉም ወላጆች እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ፈታኝአድርገውታል። በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ ስለሚሆኑ ፣ ከቤተ ዘመድ ስለሚርቁ ፣ የስራጫና እና የጊዜ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ፣ የዓለም ነጋዴዎች ልጆችን ከሃይማኖትና ከሥነ ምግባር የሚያስወጡ ተለዋዋጭ ሸቀጦችን ስለሚያጐርፉና እለት እለት ለመሳለም የሚሿት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማትገኝ የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብአድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሀይማኖትና በግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል።በዚህ ጽሑፍየቀደሙ ወላጆችን የልጅ አስተዳደግ ከቅዱሳት መጻሕፍት ለአብነት አይተን በስደት ስንኖር ልጆቻንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን በሰፊውእንዳስሳለን።
በቅዱስ መጽሐፍ ብዙ እናቶች እና አባቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ በማሳደግ በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ክብር አግኝተዋል።አባታችንአብርሃም ለልጆቹ እና በእርሱ ሥር ለሚተዳደሩት ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ እየፈጸመ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩ በማዘዝ ሙሉሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ያደረግ ነበር። በመሆኑም ይስሐቅ አባቱ አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ለሚያቀርበው መባዕመሥዋዕት እስከመሆን ድረስ ታዘዘ (ዘፍ፳፪፥፩-፲፪)።በዚህም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ ብሎ ባረከው፦ "በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገርአድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና ፣ በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፤ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋአበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና"(ዘፍ ፳፪፥፲፯-፲፰)። ልጅንበአግባቡ አሳድጎ ለሰውም ለእግዚአብሔርም ታዛዥ ማድረግ እንደዚህ በረከትን ያሰጣል።
የሙሴ እናት በስደት በነበረችበት ወቅት ለልጇ ለሙሴ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑ ወገኖቹ እስራኤላውያንየደረሰባቸውን ስደት፣ መከራ እና ስቃይ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ትነግረው ነበር። እርሱም ይህንን በልቡ አኑሮት በጎልማሳነቱ ዕድሜ የንጉሥ ልጅ ተብሎየሚኖርበትን የፈርዖንን ቤተ መንግሥት ትቶ ሄደ። ከዚያም ስደተኛ ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጐች እየጠበቀ መኖር ጀመረ።እግዚአብሔርም ከበግጠባቂነት ጠርቶ የእግዚአብሔርን በጐች ወገኖቹን እስራኤልን እንዲጠብቅ (እንዲመራ) መረጠው (ዘጸ ፫፥፩)። እግዚአብሔርም ሕዝበ እስራኤልንከግብጽ ባርነት በሙሴ መሪነት አወጣ። ታዲያ ሙሴይህንን ያደረገው ከእናቱ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እና የወገንን ፍቅር ሰለተማረ ነበር።
በአንጻሩ ግን ሊቀ ካህናት ኤሊ የራሱ ሕይወት የማይነቀፍ ቢሆንም ልጆቹ አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ፊት የማይገባቸውን በማድረጋቸውእና እርሱም እነርሱን አጥብቆ በመገሠጽ ከክፉ መንገድ እንዲመለሱ ባለማድረጉ ምክንያት በበረከት ፋንታ ሁሉም መርገም ደርሰባቸው ። እስራኤላውያን በፍልስጤማውን ተሸነፉ ፤ አፍኒን እና ፊንሐስ በጦር ሜዳ ሞቱ ፤ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፤ ኤሊም ይህን ሁሉ መከራ በሰማ ወቅትደንግጦ ሞተ (፩ኛሳሙ ፬፥፩)። የአፊኒንና የፊንሐስ ችግራቸው በእግዚአብሔር ቤት እየኖሩ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ እና የእግዚአብሔርን ቤት መደፋፈር ነበር። ሊቀ ካህናት ኤሊም ምንም እንኳን እርሱ የእግዚአብሔር ሰው ቢሆንም ልጆቹን በአግባቡ ሠርቶ ቀጥቶ ባለማሳደጉና ከክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ ባለማድረጉ ምክንያት ለዚያ ሁሉ ወድቀት ተዳረገ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይእንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርናበተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው" (ኤፌ ፮፥፩-፬) እንዳለ።ለእናት ለአባቱ የሚታዘዝ እና እድሜው የሚረዝም ልጅ ለማሳደግልጆቻችንን በመንፈሳዊ ሕይወት በፈሪሐ እግዚአብሔር ማሳደግ ይገባናል ። ያኔም አምላኩን የሚፈራ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸ ፣ ማንነቱንየሚያውቅ፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነ ፣ ለወላጆችም ሆነ ለቅድስት ቤተክርስቲያን እና ለሀገር የሚበጅ ልጅ ማፍራት ይቻላል።
ልጆቻችንንእንዴትእናሳድግ?
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይገኛሉ።ብዙ ኢትዮጵያዊም በሔደበት ሀገር ቤተሰብ መሥርቶ፣ ልጅ ወልዶ እየኖረይገኛል። በተለይ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ቊጥሩ በፍጥነት ጨምሯል ። " በመሆኑም በመላው ዓለም የተበተነው ሕዝበ ክርስቲያን ልጁንእንዴት ያሳድግ?" የሚለውን ለመረዳት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።
ሀ. ወላጆችለልጆችምሳሌበመሆን
የሥነ ምግባር መሠረትነት ያለው አርአያነትን ለልጆች የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጆች ድርሻ ነው ። ልጅ ቀጥተኛ እና የቅርብ ግንኙነትየሚኖረው ከወላጁ ጋር ስለሆነ ወላጅ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል። ለምሳሌም፦ ቃለ እግዚአብሔርን፣ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንዲሁም የሀገርንታሪክና መልካም ባሕልን ማስተማር፣የልጅን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መከታተል፣ ፍላጐትና ዝንባሌውን መገምገም፣ አስፈላጊ ነገሮችን በአግባቡማቅረብ፣ ለመንፈሣዊ ፣ አካላዊ እና ማኅበራዊ እድገቱ ሳይታክቱ መትጋት ከሁሉም በላይ ወላጅን ይመለከታል፤ቤተሰብ የመጀመሪያው ት/ቤትነው እንደሚባለው ።
በዘመናችን ልጆችን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ኮትኩቶ እና ጠብቆ ማሳደግ አንዱ መሥዋዕትነት ነው። ልጆች ሁልጊዜ የሚጥሩትወላጆቻቸውን ለመምሰል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ጢሞቴዎስ፡- "ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ" እንዳለ። (፩ጢሞ ፬፥፲፪) ስለዚህ ወላጆች በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት፣ በአለባባስእና በአነጋገር ለልጆቻቸው በተግባር ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ፍቅርን እና እንግዳ መቀበልን መልመድ ማየት አለባቸው፤ ወላጆች ይቅርታንማድረግን፣ ስህተትን ማመንን ማስተማር አለባቸው ። በተጨማሪም መዝሙርን መስማት እና መዘመር ፣ ቅዱሳት ሥዕላትን መሳለም እና በፊታቸውም መጸለይ እና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ልጆች ከወላጆች የሚማሯቸው ናቸው። በአጠቃላይ ልጆች ይህንን ካደረጉ የወላጆቻቸውነፀብራቅ ይሆናሉ ።
ለ. ልጆቻችንንወደቤተክርስቲያንበማምጣት
ቤተክርስቲያን እምነቷ እና ሥርዓቷ በሚታይ ክንውን እና በሚሰማ ጸሎትና ዜማ የሚገለጽ በመሆኑ ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ በቃልከሚማሩት ይልቅ በማየት የሚማሩት ይበልጣል።ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በትምህርታቸው እንዲህ ይሉ ነበር ፡- "ወደ ቤተክርስቲያንስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ፤አሳዩቸው፤ ሥዕሉን ይሳሙ፤ ቅዳሴ ጠበል ይጠጡ። በእምነቱ አሻሿቸውም ፤ መሰቀል እንዲስሙአስተምሯቸው። ዕጣኑን ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ቃጭሉን ይስሙ፤ ደወሉ ሲደወል ያድምጡ፤ ቄሳቸው ማን እንደሆነቤተክርስቲያናቸውም ምን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሰራ ያጥኑ"። ልጆች በቤተክርስቲያን ሲገኙ እና ሲካፈሉ ነገረ ክርስትናውን በድርጊት ፣ በማየት እና በመስማት በቀላሉ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ"ሕጻናትን ተዉአቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ፤ መንግሥተ ሰማያት እንደእነርሱ ላሉ ናትና" (ማቴ ፲፱፥፲፬) ብሎ ይቀበላቸዋል።ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕጻናት ልዩ ትኩረት አለው። (ማቴ. ፳፩ ፥፲፮) ቅዱስ ጴጥሮስን ".....ግልገሎቼን አሰማራ ..." ደግሞምሁለተኛ ".....ጠቦቶቼን ጠብቅ ..." ሦስተኛም ጊዜ "....በጎቼን አሰማራ" (ዮሐ ፳፩፥፲፭) እንዳለው። ከሰማይ ጠባቂ መላእክትን ያዝላቸዋል።"ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና" (ማቴ፲፰ ፥፲)።
ሐ. ለልጆችጊዜበመስጠት
ልጆች በሕይወታቸው ከሚያስደስታቸው ነገሮች አንዱ ከወላጆች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ነው። በተለይ ሁለቱም ወላጆች አንድ ላይ ሆነውሲጫወቱ ፣ ሲስቁ ፣ ሲመገቡ እና ሲያወሩ ማየት በጣም ይናፍቃቸዋል። በአንድ ላይ መጸለይ እና መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፣ የቤተሰብ የጋራ ጸሎት፣ የቤተሰብ አባላት በየተራ የሚያዘጋጁት ዝክር መጀመር፣ ማታ በጋራ ቅዱሳት መጽሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳዊ ፊልምችን አብሮ ማየት(የአባቶችን ታሪክ፣ የጌታችንን የማዳን ሥራ ባለው ጊዜ ውስጥ ማስተማር)። ይህም ልጆችን በእግዚአብሔር አምላካቸው መተማመንን ያሳድርባቸዋል ። ከቤት ውጪም ልጆችን የተለያዩ ቦታዎች ይዞ ወጥቶ ማሳለፍ ያስፈልጋል። መጫወቻ ቦታ፣ የእንስሳት ግቢ ፣ ታሪካዊ ቦታ፣ሙዚየም፣ ገበያ እና ወደ ቤተ ዘመድ ቤት አብሮ መሔድ ያስፈልጋል። ከዚህም ልጅ መልካም ጠባይንና ጠቃሚ ማኅበራዊ እሴቶችን ይቀስማል ።
መ. በወላጆችፍቅር አርአያነት
ልጆች ወላጆቻቸው እርስ በእርሳቸው ሲዋደዱ እና ሲተሳሰቡ ሲያዩ የደስታ ስሜት ይታይባቸዋል። በወላጆች መካከል አለመግባባት ቢኖር እንኳልጆች በሌሉበት መወያየት ያስፈልጋል። የመላው ቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ በጋራ መወያየት ልጆች ለወደፊት ችግሮችን በውይይት ለመፍታትጥሩ ተሞክሮ ይሆናቸዋል። ወላጆች በልጆቻቸው ፊት እውነተኛ መሆን ይገባቸዋል።አብርሃም ሚስቱን ሳራን እመቤቴ ይላት እንደነበር ፣ እርሷምጌታዬ ትለው እንደነበር ሁሉ ዛሬም ልጆች ከእናታቸው እና ከአባታቸው አንደበት እመቤቴ እና ጌታዬ በሚል የመከባበር ስሜት መተሳሰብን እያዩ ሊያድጉ ይገባቸዋል።
ሠ. ልጅን በመምከርእናበመገሰጽ
ልጅን መምከር የአዎንታዊ ጠባያት መገንቢያና ከመጥፎ ሥነ ምግባር ማረሚያ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "አባቶች ሆይ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርናተግሳፅ አሳድጓቸው እንጂ እንዲበሳጩ አታድርጓቸው" (ኤፌ ፮፥፲፭) ሲል ጠቢቡ ሰሎሞን "ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለ ጊዜምከእርሱ ፈቀቅ አይልም።" (ምሳ ፳፪፥፮) ብሏል። ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ "እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባትየሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ" (ምሳ ፫፥፲፩ -፲፪) እንዳለ ልጆችን ሀይማኖት እና ምግባር ይዘው እንዲያድጉ ልንገስጻቸው እና ልንቀጣቸውይገባል። በመጽሐፈ ሲራክ "ልጁን የሚወድ ሰው በእርሱ ደስ ይለው ዘንድ መቅጣትን ቸል አይልም።" (ሲራክ ፴፥ ፩) ቅጣት ሲባል ብዙ ጊዜ ወደአእምሯችን የሚመጣው አካላዊ ቅጣት ነው። ከምዕራቡ ዓለም የልጆች አያያዝ ሕግ አንጻር ግን ይህ አግባብ ላይሆን ይችላል። አካላዊ ቅጣትሳንቀጣ ልጆቻችን ከሰሩት ጥፋት ታርመው መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው የሚከተሉትን እንዲያደርጉ ወላጆች ይመከራሉ፦
ልጅየ ሚወደውን ነገር የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ መከልከል። ፊልም ማየት፣ መዝናኛ ሥፍራ መሔድ፣ ዘመድ መጠየቅ፣ . . . በጥፋቱ ምክንያትከነዚህ ነገሮች ማዕቀብ መጣል። ጥፋቱ እቃ መስበር ፣ መጣል፣ ማበላሸት ቢሆን ከራሱ በጀት ወስዶ ያንን ያጠፋውን ዕቃ መተካት። ለምሣሌለመዝናኛ፣ለተጨማሪ ነገሮች ከተመደበው፣ በሥሙ በባንክ ከተቀመጠው ገንዘብ መጠቀም እና በሠራው ጥፋት ምክንያት ጥቅሙን ማጣቱንማስገንዘብ እና እንዳይደግመው መምከር። ሁልጊዜ የሚደረግለትን ነገር በጥፋቱ ምክንያት መከልከል (አለማድረግ)።
ያደጉ ሀገሮች ስለ ልጆች መብት እና አያያዝ የጠበቀ ሕግ አላቸው። ከዚህ ሕግ ውጪ የሆነ ወላጅ ባለበት ሀገር ሕግ መሠረት ይቀጣል። የልጅ አያያዝ፣ አመጋገብ እና ጤንነት ምን እንደሚመስል የጤና ተቋማት እና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ክትትል ያደርጋሉ። በዚህ ክትትል ወቅት ልጅ ያለ አግባብ ከተያዘ ወይም ከተገረፈ የሀገሩ መንግሥት ልጁን ከወላጅ በመለየት ለአሳዳጊ ይሰጣል። ይህም በቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። ስለዚህ ወላጅ በውጪ ሀገር ልጁን በሚያሳድግበት ወቅት አጠቃላይ ስለ ልጅ አያያዝ ያለውን ሕግ እና ልጁን ሲቀጣ ስለሚያደርገው ጥንቃቄ መረዳት ይገባዋል። ከሁሉ በላይ ግን ልጅ እና ወላጅ በቋንቋ ተግባብተው ልጅ ቤተሰቡን አክብሮና ፈርቶ እንዲያድግ ከተደረገ ይህ ችግር በቀላሉ ይፈታል።
ረ. ቋንቋንእናማንነትንበማስተማር
ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች አንዱ ችግር ከልጆቻቸው ጋር የሚግባቡበት ቋንቋ ነው ። ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚናገሩት ቋንቋየሚኖሩበትን ሀገር ነው። በወላጆች የሀገሩን ቋንቋ አለማወቅ ምክንያት ልጆች የሚሰማቸውን ነገር በግልጽ ለወላጆቻቸው በሚገባ ያስረዱአይመስላቸውም ፤ ይህም በመካከላቸው ክፍተት እንዲፈጠርና ልጆችም ራሳቸውን ለወላጆች ከመግለጽ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል ። ስለዚህምበራሳቸው መኖር ይጀምራሉ። ከዚህም በላይ ወላጆች ቤተክርስቲያናቸውን እና ማንነታቸውን ለልጆቻቸው ለማስረዳት ያዳግታቸዋል። እነዚህንችግሮች ለመፍታት ወላጆች ልጆቻቸው የእነርሱን ቋንቋ እንዲናገሩ ማድረግ ከምንም በላይ አማራጭ የሌለው ነገር ነው። ልጆች የወላጆቻቸውንቋንቋ መናገር ከቻሉ ከቤተሰብ ጋር በቅርብ ይነጋገራሉ፤ ወደ ቤተሰብ ከመጣ ሰው ጋርም በፍቅር ሊነጋገሩ ይችላሉ። ይህም ማንነታቸውን እናሃይማኖታቸውን አንዲያውቁ ይረዳቸዋል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ ህጻን በተለይ ከ ፬ እስከ ፮ ዓመት ባለው እድሜ ውስጥብዙ ቋንቋዎች መማር የሚችል በመሆኑ የሚኖርበትን ሀገርም ሆነ የቤተሰቡን ቋንቋ በቀላሉ መያዝ ይችላል። ቋንቋ የማስተማር ትልቁ ሥራየወላጅ ነው ። ስለዚህ ወላጅ ማድረግ ያለበት በራሱ ቋንቋ ማናገር፣ወደ ትውልድ ሀገራቸው ልጆቻቸውን ይዘው ሄደው ከዘመዶቻቻው ጋርአብረው እረፍት እንዲያሳልፉ ማድረግ ፣ ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን የሚማሩበት መጻሕፍትን እና ሲዲዎችን መጠቀም ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያንየሕጻናት ሰ/ት/ቤት እንዲማሩ ማድረግ ነው ። የትውልድ ሀገራቸውን ቋንቋ ማወቅ ከቤተሰባቸው ጋር ለመግባባት ብቻ ሳይሆን ልጆቹ ወደፊትለሀገራቸው ለኢትዮጵያ ባዕድ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ባህላቸውን እና ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል፤ ከዚህበተጨማሪም ወደፊት በኢትዮጵያ በምርምር፣ በንግድ እና በዲፕሎማሲ ግንኙነት ሥራዎች እንዲሳተፉ ይረዳቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስ "በውኑኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጒርጒርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን" (ኤር፲፫፥፳፫) እንዳለ ሁሉ ልጆቻችን የምግባር መልካቸውእንዳይለወጥ ቋንቋቸውን እና ማንነታቸውን ማሳወቅ ግድ ይለናል።
ሰ. የዘመኑንቴክኖሎጂልጆችበአግባቡእንዲጠቀሙበማድረግ
በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ዓለምን በጣም አቀራርቧታል። በድምጽ እና በምስል ጠቃሚውም ጎጂውም ነገር በቴሌቪዥን፣ በድረ ገጽ፣ በእጅ ሰልክ፣በመጽሔትና በጋዜጣ በየትኛውም ቦታ ይገኛል። እነዚህ የሚዲያ ውጤቶች በተለይ ባደጉት ሀገሮች ለልጅም ሆነ ለአዋቂ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው።ልጆቻችን የሚያዩትን ፣ የሚሰሙትን እና የሚያነቡትን ነገር ጠንቅቆ ማወቅ እና መቆጣጠር ያስፈልጋል። በተለይ በቴሌቪዥን የሚያዩትን ነገርለይቶ ማወቅና ጊዜ መገደብ ያስፈልጋል። በተጨማሪ ቴሌቪዥንን በአግባቡ ካልተጠቀሙ ፣ በፊልም የሚያይዋቸውን ወንጀሎች እየተለማመዱወደ ማከናውን ይመጣሉ ፤ ለምሳሌ ስርቆት፣ አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ፣ መደባደብ ... ። በሚዲያ የሚተዋወቁ የመንገድ ላይ ምግቦች (fast foods) በማየትም ለጤና ጎጂ ለሆኑ ምግቦች ልዩ ፍቅር ይኖራቸዋል። ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋርስለሚያሳልፉ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ስለማይገናኙ የብቸኝነትን (ግለኝነት) ሕይወት ይለማመዳሉ። ይህንን ለመከላከል ወላጆች ሰለዘመኑ ቴክኖሎጂበቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። በቤት ውስጥም የወላጅ መቆጣጠሪያ (Parental control) በኢንተርኔት መስመር ላይ መጠቀም ይኖርባቸዋል።እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች ችግሩን ቢያቀሉትም ፣ ፈጽሞ እንዳይከሰት ማድረግ ግን አይችሉም። ከእነዚህ መፍትሔዎች ጋር የበለጠ ውጤታማለመሆን ልጆችን በጉዳዩ ዙርያ ጥቅም እና ጉዳቱን ለይቶ ማስተማር እና ከወላጅ የተደበቀ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል።
ማጠቃለያ
በውጭው ዓለም
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስደቱ በአንጻራዊነት በቅርብ ዓመታት በመሆኑ ብዙዎቹ ልጆች ታዳጊ ናቸው ። ስለዚህ ለሚቀጡሉት አስር አመታት ልጆቻችን ቤተክርስቲያናቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ፣ በትምህርታቸውም እንዲጠነክሩ ካደረገንአዲሱ ትውልድ በሃይማኖት እና በምግባር የታነጸ፣ አምላኩን የሚፈራ፣ ማንነቱን የሚያውቅ፣ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነና መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስም የተዘጋጀ ይሆናል::
በስደት ስንኖር ለልጆቻችን ልናወርሳቸው የምንችለው ትልቅ ሀብት እግዚአብሔርን መፍራት ነው። በአሁን ወቅት ዓለም ለክርስቲያኖች ፈታኝመድረክ ነች። ይህን ፈተና ለመወጣት ትልቁ ሀብት ደግሞ ፈሪሐ እግዚብሔር ነው። ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው ሰው ጥበብ ይሰጠዋል። "የጥበብመጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው" (ምሳሌ፯፥፩) እንዲል። ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው ሰው መላእክት በዙሪያው ይሰፍራሉ፤ ያድኑትማል ።(መዝ፺፥፲፩) እንደ ዮሴፍ ወደ ኅጢአት በተጋበዘ ወቅት "ሰው ባያይ እግዚአብሔር ያያል።" (ዘፍ፴፱፥፯-፲፫) ይላል ። ስለዚህ በልጆች አስተዳደግጠንክረን መስራት እና ፈሪሐ እግዚአብሔርን ማስተማር ያለብን ዛሬ ነው።
ዋቢመጻሕፍት
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፦ መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ። ፲፱፻፹፱ ዓ.ም.
ፈሰሴ ገ/ሃና ፣ በላቸው ጨከነ ፡- የልጆች አስተዳደግ በዚህ ዘመን ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች። ሎንዶን፳፻፮ ዓ.ም.
ማኅበረ ቅዱሳን ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፳ኛ ዓመት ቁጥር ፬ ነሐሴ ፳፻፬ ዓ.ም.
ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር፡- ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ እና የልጆች አስተዳደግ። አኮቴት አሳታሚዎች አዲስ አበባ። ፳፻፬ ዓ.ም.
*ኢጲፋኒያ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በታላቋ ብሪታኒያ ለበዓለ ጥምቀት በተዘጋጀ ልዩ ዕትም ላይ የታተመ። የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም.